ፖርኩን በመጎብኘት ኮርያ የዘመቱ ጀግና ኢትዮጵያዊ ወታደሮችን ታሪክ ይወቁ!!
ኢትዮ ኮርያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ ቀድሞ አፍንጮ በር ፓርክ በሚል ይታወቅ የነበረ ሲሆን በ1995ዓ.ም በኮሪያ ለዘመቱ መታሰቢያ እንዲሆን በሚል ስያሜው ተቀይሯል።
ኢትዮጵያ በኮርያ ጦርነት እንድትሳተፍ በተባበሩት መንግስታት በቀረበላት ጥያቄ መሰረት እ.ኤ.አ ከ25/5/1950 እሰከ 27/7/1953 ድረስ በተካሄደው የኮርያ ጦርነት ላይ የኢትዮጵያ ተዋጊ ሀይሎች ለአለም ሰላምና ነጻነት ሲሉ በዚች መሬት ላይ በጀግንነት እና በቆራጥነት ተዋግተዋል።እስከ ጦርነቱ ማብቂያ ድረስ ከአፍሪካ ግዛት ውስጥ ወደ ኮርያ ጦርነት 6037 የንጉስ የክብር ዘብ ወታደሮቿን በፈረቃ የላከች ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ስትሆን በዚሁ ጦርነት በሶስት ዙር ከዘመቱት ብቻ 121 በግዳጅ ላይ ሲሞቱ 536 የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ወታደሮቹ በ32ኛዉ ሬጀመንት 7ኛው የአሜሪካ ዲቪዥዮን ስር ሆነው በሻንያንጊኒ አጠገብ በቾኩምሳን ካነግዎን ግዛት በፖንች በውል በመንዳንግኒ ሸለቆዎች በኩመሀዋ በአይረን ትሪአንግል እንደ ቾምዮን ካሚል እና ፖርክቾክ ተራራ ላይ 253 ጦርነቶችን አካሄደዋል።በተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ ኢትዮጵያ አንድም ወታደር አልተማረከባትም።የኢትዮጵያ ጦር በጦርነቱ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጾ በአሜሪካ እና በኮርያ ሪፐብሊክ ኘሬዝዳንቶች ሽልማት ተበርክቶለታል። አኩሪ ታሪኩ በአለም ለዘላለም ሲዘከር ይኖራል።